torsdag 28. mai 2015

ህወአትን እያጠቁ ከኦህዴድ ጋር እየተሞዳሞዱ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል የትም አያደርስም.

በሀገራችን ውስጥ በሁሉም መስክ የህወአት የበላይነት እንዳለ ይታወቃል። በኢህአዴግ ውስጥም ህወአት የበላይ ነው። ኦህዴድም ሆነ ደህኢህዴን ተጠፍጥፈው የተሰሩት በህወአት ነው። ነገር ግን ያ ማለት በሚፈጸሙት ወንጀሎች ውስጥ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን የሉበትም ከተጠያቂነትም ነጻ ናቸው ማለት አይደለም። በተፈጸሙት ግድያዎች፣ ሰዎችን ማሰርና ማሰቃየት፣ ማሳደድና ማፈናቀል፣ የመሬት ወረራ፣ ሙስና ወዘተ. እኩል ተጠያቂ ናቸው። ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ይሄንን አያለው ለኦሮሞ መብት ከሚታገሉ ወገኖች ውስጥ የተወሰኑት ለህወአት ያላቸውን የመረረ ተቃውሞ ያህል ለኦህዴድ የላቸውም። በጣም ተለሳልሰውና ነገሩን ቀለል አድርገው ነው የሚያዩት። አንዳንዶቹም በኦህዴድ በኩል ተጠቅመን ህወአትን ከሥልጣን እናባርራለን ኦሮሚያንም ነጻ እናወጣለን የሚል እምነትና ተስፋ አላቸው። እንቅስቃሴያቸውን በቅንነት በመውሰድ እስኪ የሚሆነውን ነገር ልመለክት በሚል ምንም ማለት አልፈልግም ነበር።
አሁን ግን ከዚያም በላይ ከፍ ብለው ትናንትና “ገዳይ ነው በሀገራችን አላኖር አለን” ብለው ከሀገር ካሳደዳቸው ባለሥልጣንና “ተቃወሙት መሬታችሁን እንዳታስነጥቁ” ብለው ቀስቅሰው በርካት ወጣቶች ወደ አደባባይ ወጥተው ሲቃወሙ አብሮ ተማሪዎችን ካስገደለ፣ ካሳሰሰረ. . .ሰው ጋር አብረው በአንድ ጠረቤዛ ላይ ፈታ ሲሉ ሳይ ይሄንን ለማለት ፈለኩኝ። እንደ ኦሮሞ አክቲቪስትነታቸው በደንብ ተደራጅተው የሥርዓቱን ቁንጮ ደም አፍሳሾች፣ አምባ-ገነኖችና ሙሰኞችን ይቃወማሉ ብዬ ስጠብቅ አብረው ዘና ሲሉ ማየት በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል። የሚያዩት የጨቋኞቹን ብሔር ነው ወይስ ድርጊት? አንድ ሰው ቢረግጠኝም የእኔ ብሔር አባል ከሆነ በልዩ ሁኔታ ልቀርበውና ልንከባከበው ከሌላ ብሔር ከሆነ ግን ጠላት አድርጌ ላሳደደው ነው ማለት ነው?
አንድ እውነት አለ። ህአወት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን ነገር ቢቆጣጠርም ከሥር ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ ኦሮሚያ ላይ አሁን ያሉት የኦሮሞ ብሔር አባላት ናቸው። ከላይ ህወአት ለሚያስተላልፈው ትዕዛዝ አብረው ተስማምተው ኦሮሞውን ኦነግ፣ ሽብርተኛና ጠባብ እያሉ የሚጠቁሙ፣ የሚያሳስሩ፣ የሚያስገርፉ ወዘተ. ራሳቸው ኦህዴዶች ናቸው። እናም በምን ስሌት ነው አብሮ የሚገድለውን ትተህ ትዕዛዝ ሰጥቷል ብለህ የምታመነውን ብቻ የምትቃወመው? እኔ በሀገር አቀፍ ጉዳይ ላይ ስለማተኩር በብዛት ህወአትን ላይ አተኩራለው ይሄንን ሳደርግ ግን የተቀሩትን አጋር ፓርቲዎች ድርሻና ሚና በመርሳት አይደለም። ኦሮሚያ ላይ ብቻ ባተኩር ኖሮ በርካታ ነገሮችን ከኦህዴድ ጋር አያይዤ ባቀረብኩኝ ነበር።
ኦሮሚያ ክልልን በደንብ አውቀዋለው። ምን ይካሄድ እንደነበር የኦህዴድን አሰላለፍ ጭምር ምን እንደነበር፣ ከየት አካባቢ ያሉት ሰዎች የበለጠ እንደሚጠጉ የትኞቹ በጥርጣሬ እንደሚታዩ አውቃለው። አንዳንዶች እዚህ ፌስቡክ ላይ ሌላ ሰው ምንም እንደማያውቅ አድርገው ስለ ኦሮሚያ ክልል የሚናገሩት ውሸት አለ። በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን ደረጃ የኦሮሞን ሕዝብ በጭቆናና በሙስና ደም እያስለቀሱ ያሉት ሕሊናቸውን በጥቅም የሸጡ ኦህዴዶች ናቸው። ህወአት በያንዳንዱ የቀበሌ ውሳኔ ውስጥ ሁሉ ገብቶ እየፈተፈተ አይደለም። እንግዲህ አሁን ለእነዚህ ተባባሪ ወንጀለኞች ነው የተለሳለሰ አቀራረብና አቋም ለማሳየት እየተሞከረ ያለው። ይሄ ለእኔ መሞዳሞድ ነው። ጥያቄው በትክክል ለነጻነት፣ ለፍትህና፣ ለዕኩልነት ከሆነ ለህወአትም ሆነ ለኦህዴድ ዕኩል አመለካከት ይዘህ ትታገላለህ እንጂ ህወአትን ጠላት አድርገህ ፈርጀህ ለኦህዴድ የተለየ ርህራሄ አታሳይም። ጥያቄው ግን የሥልጣን መጋራት ከሆነ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው።
ሌላው በኦህዴድ በኩል ህወአትን ከሥልጣን አባርራለው ማለት ሊሰራ አይችልም። ምክንያቱም አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኦህዴድ አመራሮች ወዶ ገብና የጥቅም ተጋሪዎች ናቸው። ለኦሮሞ ብሔር የሚቆረቆሩ ቢሆኑ ኖሮ የኦህዴድ አባል አይሆኑም ነበር። ስለዚህ ለማን ብለው ነው ለጥቅም ብለው ከገቡበትና ጥቅሙን እየተቋደሱ ያሉበትን ድርጅት የሚቃወሙት? አንዳንዶች ድንገት ሕሊና ካላቸው ይላሉ። ሕሊና ቢኖራቸውማ መጀመሪያ ነገር አባል አይሆኑም ነበር። በተደጋጋሚ የኦሮሞ ሕዝብ እየታሰረ፣ እየተገደና እየተፈናቀለ እያዩ ምን አደረጉ? ምንም።
በኦህዴድ በኩል ህወአትን ከሥልጣን አባርራለው ብሎ ለኦህዴድ ልዩ የሆነ አቀራረብ መከተል በጣም የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ በኦሮሞ ሕዝብ መከራና በደል ላይም ማላገጥ ነው። በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የሌሎቹ ፓርቲዎች መሪዎች ህወአትን ተቃውመው ሊነሱ አይችሉም። ምን አልባት የሆነ ስብሰባ ላይ የሆነ ጥያቄ ሊጠይቁ ወይም ሊያጉረመርሙ ይችላሉ። ነገር ግን በማግስቱ እጃቸውን አውጥተው ከመወሰንና አብሮ ከመስራት ውጪ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። ሲያደርጉም አልታዩም። አብረው መቀጠል ያልፈለጉት ደግሞ ወደተቃውሞ ወገን ተቀላቅለዋል ወይም ሀገር ጥለው ወጥተዋል። ያላቸው አማራጭ ይሄ ነው። እናም ገና ለገና ኦህዴድን የሚመሩት ኦሮሞች ናቸውና ህወአትን ለማባረር በማደርገው ትግል ይረዱኛል ብሎ መጠበቅ የተሳሳተ ስሌት ነው። ቢሰራ ኖሮ ገና ድሮ እነሱ ራሳቸውን ነጻ አውጥተው የኦሮሞንም ሕዝብ ነጻ ያወጡ ነበር።

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar