ሌቦክራሲ የሚለው የፖለቲካ ስርዓት ስያሜ የወያኔን ከ “ነጻ አውጭ ነት” ወደ ሌብነት ስርዓት መመስረት ያደረገውን ሽግግር አመልካች ነው። የሌቦች አገዛዝ ለማለት ነው። ሌቦክራሲ በስልጣን የባለጉ፤በሙስና የተዘፈቁ የሚመሩት ስርዓት ነው። በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከስልጣን ወጥቶ እንዲህ የህዝብ ንብረት በድፍረት የዘረፈበት ታሪክ የለም።እንዲህም አድርጎ ህዝብ ያፈነ ስርዓት አልነበረም። ይህ ምርጫ የሌቦች ስም ማደሻ ሰልፍ ማስተካከያ እንጂ ሌላ አይደም።የዚህ ስያሜ የሰጠነው ስርዓት እሰነብትበታለሁ የሚለው ትዕይንት ነው።የምናውቀው እባብ አዲስ ቆዳ የሚለብስበት።
አፍ ተሸብቦ፤ በግድ ምረጥ ብሎ፤ ካልመረጥ ደግሞ “ይከተልሃል” ተብሎ ምን ምርጫ ይባላል? ግዳጅ እንጂ።የቀድሞ ታዛቢ ያፈረበት፤ የተቸበት ምርጫ በኢትዮጵያ እየተካሄድ ነው። ህወሃት መሩ መንግስት ያለሀፍረት ተመረጥኩ፤ ህዝቡ እምነቱን ሰጠኝ ብሎ ለመደንፋት እየተመቻቸ ነው።
መጀመሪያ ዲሞክራሲን ምርጫ፤መመረጥ፤በየአራት፡ አምስት ዓመት፡ የሚመጣ፤ የሚሄድ አድርገን እንዳናይ በኛው ታሪክ እንኳን ቢያንስ የሁለት ዓሰርት ዓመታት ልምዳችን በቂ ትምህርት ሰጥቶናል።ከወያኔ ስርዓት ሌላ የነበረውን ትተን ማለት ነው።በምርጫ መሪዎች ማውጣት፤በምርጫው ጊዜ በሙሉ ፍላጎትና ስሜት መካፈልን አስመስክረናል።ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ ስርዓት ናፍቆታቸውን የሁለት መቶ ዓመታት ልምድ አለን ከሚሉት ለምሳሌ አሜሪካ እንደማናንስ አሳይተናል።ኢትዮጵያዊው መራጭ ማለዳ የወጣ ጀምበር እስክትጠልቅ ድምጹን ለመስጠት ተራውን በመጠበቅ ጽናቱን አሳይቷል።
ዲሞክራሲ የሚገነባ ስርዓት ነው።ሸፍጠኞችም የሚያንጹት አይደለም።ላገር ለህዝብ የሚሉ ከዝቡ ጋር ሆነው የሚያቆሙት ያገር መውደድ ፍሬ እንጂ ለወሬ ፍጆታ የሚቀርብም አይደለም።ዲሞክራሲ የባህል ለውጥ ማዕከል ነው።መከባበርን ወግ የሚያደርግ ነው።ለአገር እድገት መሰረት ነው።በህግ መገዛትን መሰረት ያደረገ ነው።የሰው አክብሮት፤ፈሪሃ እግዚአብሄርም አጥሩ ነው። እውን ጠባብ ብሄርተኞች፤ክፋትና ጥላቻ አስፋፊዎች ዲሞክራሲን ያበስራሉ ? ህወሃት መሩ መንግስትና ዲሞክራሲ ተቃራኒዎች ናቸው።
ዛሬ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ትእይንት የምርጫ አቸናፊው ቀድሞ የታወቀበት ነው።እግር ተወርች የታሰረ ተወዳዳሪ ጡንቻውን ሊያሳይ ሁሉን ከሚያደርግ የመንግስት ፓርቲ ጋር ይወዳደራል። ይህ መሆኑን በግልጥ እያወቁ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ ምርጫ ይደረጋል ብለው ሲመሰክሩም ታዝበናል።ምርጫማ አፍሪካ ሁሉ ያደርገው የለ? በአሜሪካ መንግስት አስተያየት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያደገ፤እየጎለበተ ነው። ይህን ያለ አምባገነን ሁሉ የሚያካሂደው “ውድድር” መልካም ነው እንደማለት ነው። እንኳን አሁን ፋሺሽት ኢጣሊያም ስትወረን ማን ከማን ጋር እንደቆመ የሚሳየው ታሪክ የሩቅ ጊዜ አይደለም።ኢትዮጵያ በውጭ ወዳጅ የታለች ሆና አታውቅም።ወዳጅ አለኝ ብለው ካልተማመኑት አባቶቻችን ለመማር ጊዜ የሚወስድ አይደለም። ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ያለው ታሪካችን ብቻ በቂ ትምህርት ይሰጣል።
ሰሞኑን በቡሩንዲ ሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ህጉን የቀየረውን መሪ ህዝቡ ለመቋቋም ሲታገል ተመልክተናል። “አታረጋትም !” ብሎ ሆ ብሎ ወጥቷል።ይህ እምቢታ ዛሬ ተሳካ አልተሳካ የጊዜ ጉዳይ ነው።የቡሩንዲ ህዝብ መልክቱን አስተላልፏል።በሚካሄደው የህወሃት የምርጫ ቲያትርም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለውን እየጠበቅን ነው።የጠላውን፤ያንገሸገሸው፤ያስመረረው የህወሃት መንግስት “ከነምርጫ ቲያትርህ ጥርግ በል” ሊለው ይችላል። ከዚህ ከውጭ ያለነው የምንታዘበው የኢትዮጵያ ህዝብ በትዕስግቱ፤እየደማ፤ እየታሰረ፤ሰብዕናው እንዲደፈር ቢደረግም ህወሃት መሩ መንግስትን ዛሬ አዳከሟል:: የውጭ ሀይሎችን የሙጥኝ እንዲል አድርጎታል። ህወሃት መሩን መንግስት በስርቆት ፋፍቶ መንቀሳቀስ የማይችል ዝሆን አድርጎ አዝሎታል።ገፍትሮ የሚጥለው ጊዜ መቃረቡን አመልካች ምክንያቶች ብዙ ናቸው።
ይህ ምርጫ ወትሮ ከሚደረጉት ልዩ የሚሆንበት ካጀቡት ሁኔታዎች አንጻር ሲታይ ነው።ወያኔ ሙሉበሙሉ የዲፕሎማሲ ክስረት እያናጋው አይደለም።የስለላ መዋቅሩ በትላልቅ ከተሞች አስልቷል።ተቃዋሚዎች በአድጎራ መቆም እየጀመሩ እንጂ ገና በህብረት በጥንካሬ አልቆሙም። ይህም ቢሆን ግን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ህዝባዊ አመጽን የሚጭር ሁኔታ ቢከሰት ቶሎ የሚቀየር፤ መንግስቱን የሚያርድ ሁኔታ አይፈጠርም ማለት አይደለም።የንጉሳዊ ስርዓትና ደርግን የሸኗቸው ምክንያቶች በጣም ጨምረው ዛሬ በአገራችን ይገኛሉ። የኑሮ ውድነቱ ለከት የለውም::ወጣቱም ሆነ ሌላው ተስፋ ቆርጧል። የህዝቡ እሮሮ አንገሽግሿቸው ወያኔ በሚያውቀው መንገድ ሊገጥሙት የቆረጡ ህዝቡን አይዞህ የሚሉት ሀይሎች መኖር ዋናው ነው። ይህን ህወሃት መሩ መንግስት አታንሱብኝ ብሏል።በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆች በቁጭት ለተግባር መነሳታቸው አንዱ ትልቅ ክስት ነው።በኢትዮጵያ ህዝቡ በሚችለው ሁሉ በከተማ በገጠር ይህን የክፋት ስርዓት እየተቋቋመ ነው።የሌቦክራሲው ስርዓትን የሚሰናብቱ እኒሁ ሶስት ረድፎች ናቸው።የህዝብ ትግል በከተማ በገጠር፤በውጭ ያለነው እርዳታ፤ህወሃት መሩን መንግስት በሀይል እያጫነቁት ያሉት ወንድሞቻችን ጽናት አይነተኛ ነው።ከነዚህ ሀይሎች ማንም ደገፍኩህ ቢለው የህወሃትን መንግስት ሊያሰነብተው አይችልም።
በመጨረሻ ይህ ምርጫ ሲያልፍ ያው የተለምዶው ይቀጥላል እንጂ ወዲያው የሚቀየር ነገር ይኖራል ማለት ዛሬ አይቻል ይሆናል።አንድ ትልቅ ትምህርት ግን ትቶ ያልፋል። ህወሃት መሩ መንግስት በሰላም፤በምርጫ ይቀየራል የሚሉትን ግንዛቤአቸው ቀይሮ ያልፋል። ይህ ደግሞ ለወሳኙ ፍልሚያ ጠቃሚ ነው። ወያኔን አንበረካኪ ሁኔታ ሳይኖር የሰላም ሽግግር የማይሆን መሆኑን አስገንዝቦ ማለፉ ለዲሞክራሲ ትግላችን ያቀረበው ትምህርት ይሆናል።
ምርጫን ለህዝብ ቅንጣትም ደንታ የሌላቸው መንግስታትም ያደርጋሉ። ወጉ ምርጫ መካሄዱ ሳይሆን እንዴት ባለ ስርዓት ተካሄደ ነው።ምርጫ ሲደረግ ህዝብ የወደደውን ያሰነብታል።የጠላውን ያሰናብታል።ሁሉም በስልጣን ያለ “ተመርጨ ነው” ማለትን ይወዳል።ተመረጠ ተወደደን አመልካች በመሆኑ።ለዚህ ገና አልታደልንም።የተቀናጀ ትግል ይጠይቃል።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar