May 1, 2015
በየመን፣ በደቡብ አፍሪካ እና በሊቢያ ውስጥ ባሉ ኢትዮዽያን ላይ የተፈፀመውን መጠን የለሽ ግፍ በማውገዝ ኢትዮዽያውያን በኖርዌ ሰልፍ ወጡ።
ሰልፉ የተዘጋጀው በኢትዮዽያ ስደተኞች ማሕበር በኖርዌይ አስተባባሪነት ሲሆን ሁለት ዓይነት ዓላማዎች ነበሩት ይኸውም፣
1ኛው:- ሐገራት ዜጐቻቸውን ከየመን ጦርነት ሊያሸሹ ትራንስፖርት ለመላክ ከላይ እታች ሲሉ ኢትዮዽያንን እወክላለሁ ብሎ የሚቀባጥረው ወያኔ ስልክ ደውሉ ሲል ማሾፉውን፤በሊብያ አይሲሲ ኢትዮዽያውያንን አረድኩ ብሎ እየተናገርና የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ እነ አሜሪካ የሐዘን መግለጫ እየላኩ ባለበት ወቅት ኢትዮዽያዊ መሆናቸውን ለማጣራት እየሞከርኩ ነው ብሎ የተሳለቀውን ፤ በደቡብ አፍሪካ ከነሕይወታቸው በእሳት ሲቃጠሉ እንደሐገር መሪ ይሕ ነው የሚባል መልስ ያልሰጠውን ወያኔ ለማውገዝ እና
2ኛ:- ኢትዮዽያውያንን ከውርደትና ከጥቃት ሊከላከል የሚችል ለኢትዮዽያውያን የቆመ መንግስት በኢትዮዽያ ስለሌለ በሊቢያ፣በየመን፣በደቡብ አፍሪካ በሞት አፋፍ ላይ ያሉትን ኢትዮዽያዉያንን ሕይወት የዓለም መንግስታት እንዲታደጉ ጥሪ ለማድረግ ሲሆን ፤የሐገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ስሜትና መሪር ሐዘን የተገለፀበት፤የወገን ተቆርቋሪነት የታየበት ነበር።
በኢትዮዽያውያን ላይ እየደረሰ ላለው መከራና ስቃይ ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ የተባለው፤ከትግራይ ነፃ አውጭነት ስሙን እንኩዋን መቀየር ሳይችል 24 ዓመት በሙሉ በኢትዮያውያን ጫንቃ ላይ ተቀምጦ ኢትዮዽያን እያፈረሰና ሕዝብ እየጨፈጨፈ ያለውና እራሱን መንግስት ነኝ ብሎ የሚቆጥረው የወያኔ ቡድን በመሆኑ እንደዜጋ ተከብሮ ለመኖር ወያኔን ለመጣል የእያንዳንዱ ኢትዮዽያዊ የትግል አስተዋፆ ወሳኝ እንደሆነ ገልፀው በየመን ፣በሐገር ቤት በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ባሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ላይ የተፈፀመውን ግፍ በመቃወም የተሰማቸውን መሪር ሐዘን ለመግለፅ ሰልፍ በወጡት ኢትዮዽያውያን ላይ በወያኔ የደረሰውን ድብደባና እስር በማውገዝ የኢትዮዽያው አይ ሲ ሲ ሲሉ ገልፀውታል።
ምቹ ሕይወቱን ትቶ ለኢትዮዽያ ሕዝብ ነፃነት፣ ፍተሕና እኩልነት የታገለውን የኢትዮዽያ ማንዴላ አንዳርጋቸውን ለእኩይ ተግባሩ ፕሌን የላከው ወያኔ በየመን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮዽያንን ከጦርነት ለመታደግ ያልምከረው ለሕዝብ ዴንታ ስለሌለዉ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ሰልፈኞቹ በመፈክራቸው የዓለም መንግስታት ኢትዮጵያውያንን በማሸበር ላይ ያለውን ወያኔ ከመርዳት እንዲታቀቡ ያሳሰቡ ሲሆን በተጨማሪም፤
አለማቀፉ ሕብረተሰብ በሊብያ፣ በየመን እና በደቡብ አፍሪካ ችግር ውስጥ ላሉ ኢትዮዽያውያን እንዲደርስላቸውና በኖርዌ ያሉ ኢትዮዽያውያን ስደተኞችን ጉዳይ የኖርዌ መንግስት ባግባቡ እንዲያይ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኖርውጃን ፓርላማ ከተሰጠ በሁዋላ በሰልፉ ላይ የተለያዮ ድርጅት ተወካዮች ንግር ያደረጉ ሲሆን ዶክተር ሙሉ ዓለም፣ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮዽያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ም፨ሊ አቶ ዳንኤል አበበ፣ የአዲስ ቃል ኪዳን ፈውስ አገልግሎት ሚኒስትሪ አገልጋይ ወ/ሮ ሰዋሰው ስለሺ አቶ ሐሰን መሐመድን ይዘው እኛ የኢትዮዽያውያን ሙስሊሞችን እና ክርስቲያኖችን ወክለን አብረን ቆመን እንፀልያለን ፤በኢትዮዽያ ሙስሊምና ክርስቲያኖች መካከል ምንም ችግር የለብንም ፤አይ ሲ ሲ የኢትዮዽያን ሙስሊም አይወክልም እኛ አንድ ነን ብለው ከሰልፈኛው ጋር በኖርውጃውያን ፓርላማ ፊት ለፊት ተንበርክከው ወደፈጣሪያቸው አቤት ያሉ ሲሆን እግዚአብሄር ግፈኞችን እንዲያስወግድ ተማፅነው ፤የእምነት ሰዎች ነን እያሉ እውነቱን በመደበቅ በእግዚአብሄር እየነገዱ ያሉትም የእምነት ሰወች ተወቅሰዋል። ሰልፈኞቹም በወገኖቻቸው ላይ በደረሰው ግፍ የተሰማቸውን መሪር ሐዘን በለቅሶ ሲገልፁ ታይተዋል።
ዘወትር በሐገራቸው ጉዳይ ላይ ወደሁዋላ የማይሉት አቶ አምሳል ካሴም ፪፬ ዓመት ኢትዮዽያን እያወደመ ያለውን ወያኔ ከስልጣን ለማስወገድ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት፤ በሐገር ቤትም በውጭም ኢትዮዽያውያን እየተጨፈጨፉ የችግራችን ምንጭ የሆነውን ወያኔ ለመጣል የማይነሳ ሁሉ ተጠያቂ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮዽያ ስደተኞች ማሕበር በኖርዌም በሰልፉ ላይ የተገኙትን በሙሉ አመስግኖ ዘወትር ማሕበሩ በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ከጐኑ በመቆም ታላቅ አስተዋፆ እያበረከቱ ያሉትን አቶ ዩሐንስ አበራን ከልብ አመስግኗል ።
የኢትዮዺያ ስደተግኛ ማህበር በኖርዌ
ዮናስ ታምሩ
ህዝብ ግኑኝነት
ህዝብ ግኑኝነት
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar