tirsdag 23. juni 2015

“ባቡሩ ጣቢያ መኖሩን እንጂ እዚያ ለመድረሱ እርግጠኛ አይደለም”

በ1994ዓም የኢራቁ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን “በምርጫ” 100% ደፍነው ነበር፡፡ ያለፈው ዓመት ደግሞ የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ-ኧን ያለአንዳች ተቀናቃኝ ባደረጉት “ከፍተኛ ትንቅንቅ” በነበረበት የምርጫ ውድድር ብቻቸውን ተወዳድረው በመጨረሻው ላይ ትንፋሻቸውን ይዘው 100% ለመድፈን በቅተዋል፡፡
ሳዳም 100 ከደፈኑ በኋላ ብዙም አልቆዩም፡፡ በሌላ በኩል የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ታላቁ ባለራዕይ መሪ ኪም ጆንግ ኢል ከልጃቸው ኪም ጆንግ-ኧን በ0.1% በመበለጥ በ2001ዓም 99.9% ያገኙ “ጎበዝ” ነበሩ፡፡
የኩባው ራዑል ካስትሮ በ2000ዓም 99.4% ሲያገኙ የሶሪያው ባሽር አል አሳድ 97.6% ያስቆጠሩ ሌላው “ደፋኝ” ናቸው፡፡ የቱርክሜኒስታኑ ሳፓርሙራት ኒያዞቭ በ1984 እንዲሁም የቼችኒያው የተባበሩት ሩሲያ ፓርቲ በ2003ዓም 99.5% ያስቆጠሩ ሌሎቹ “ጎበዞች” ናቸው፡፡ በ1996ዓም በጆርጂያ ሚኻኤል ሳካሽቪሊ ሌላው 96% ያገኙ ታታሪ “ተመራጭ” ናቸው፡፡
በአምባገነን አገዛዞች ውስጥ የሚደረግ ምርጫ አንድ ተወዳዳሪ ራሱን በማቅረብ የሚወዳደር ከመሆኑ ባሻገር መራጮች የሚሰጣቸው ምርጫ አምባገነኑን መምረጥ ወይም ስቃይና መከራ መቀበል ነው፡፡ አንዳንዶቹ አምባገነኖች “ፉክክር” ተደርጎ ነበር ለማስባል “ታማኝ ተፎካካሪዎችን” ራሳቸው እንደሚፈጥሩና “ምርጫው ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላ” እንዲመስል እንደሚያደርጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑት ቶማስ ሉንድበርግ ሲናገሩ “ከሁለት ሦስተኛ በላይ ድምጽ አግኝቶ በማንኛውም ምርጫ የሚያል (ፓርቲ) ሲኖር ጥርጣሬ ሊያስነሳ ይገባል” ብለዋል፡፡ ምክንያቱን ሲጠቅሱም በፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ይህ ዓይነቱ ውጤት ያልተለመደ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ የተበታተኑ (ኅብረት ያልፈጠሩ) የተቀናቃኝ ፓርቲዎች በሚኖሩበት ምርጫ የሚገኘው ውጤት 60-80% ሊያልፍ አይችልም ይላሉ፡፡
አምባገነናዊ ሥርዓቶች የሚጋልቡት ባቡር የታሰበበት መድረሻ እንደሚደርስ አምባገነኖቹ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ባቡሩ የሚያውቀው ጣቢያ መኖሩን ብቻ ነው፡፡ አልፎ ስለመጣው ሃዲድና መሰል ጉዳዮች የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም፡፡ መድረሻ ጣቢያ እንዳለው ያውቃል፤ አሁን ካለበት ጣቢያ እስከመድረሻው ጣቢያዎች እንዳሉ ያውቃል፡፡ የመጨረሻ ጣቢያ ስለመድረሱ ግን ምንም በእርግጠኝነት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሃዲዱ እየሰራ ይሁን፣ ያደርሰው ይሆን፣ መንገድ ላይ አደጋ ይኑር፣ … ምንም እርግጠኛ ሆኖ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡
“ስለ ክብር አልባ ታላቅነት፣ ጥበብ አልባ ሃብት፣ ሕግ አልባ ኃይልና ሥልጣን ታሪክ ምን ይላል? መልሱ በባቢሎን፣ በሜዶንና ፋርስ፣ በግሪክ እንዲሁም በሮም ታላላቅ ግዛተ አጼዎች መገርሰስ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ እነዚህ አራት ተከታታይ ዓለምን የገዙ ኃያላን ነበሩ፡፡ አሁን በምን ሁኔታና የት ይሆን ያሉት?” ኦርሰን ኤፍ ዊትኒይ፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar