mandag 22. juni 2015

በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ዳና ቶራ ቀበሌ የኢማዴ-ደህአፓ/መድረክ መሠረታዊ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃኑ ረቦ ተገደሉ

 በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ዳና ቶራ ቀበሌ የኢማዴ-ደህአፓ/መድረክ መሠረታዊ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃኑ ረቦ ተገደሉ፡፡
በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ በዳና ቶራ ቀበሌ ነዋሪና የኢማዴ-ደህአፓ/መድረክ መሠረታዊ ኮሚቴ አባል የነበሩትና በ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ በቅስቀሳ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከፍተኛ አስተዋጾ ሲያበረክቱ የቆዩት አቶ ብርሃኑ ረቦ ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ በመኖሪያ መንደራቸው በተፈጸመባቸው ድብደባ ከተገደሉ በኋላ ወንዝ ውስጥ ተጥለው ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ ይኼው የመድረክ አባሉ ከመገደላቸው በፊት ብርሃኑ ደቦጭና ታዲዮስ ጡምሶ የሚባሉ ፖሊሶች ሟቹንና ሌሎች በቀበሌው የሚኖሩ የመድረክ አባላትን ለመደብደብ ሲያሳድዱ ሟቹ ከአከባቢው ሸሽተው የሄዱ ሲሆን ሌሎቹን አባላት አግኝተው መደብደባቸውና እርሳቸውን ሲፈልጉ ካመሹ በኋላ ማታ ወደቤታቸው ሲመለሱ ጠብቀው ግዲያውን ፈጽመው ወደ ወንዝ ወስደው እንደጣሉ ከአከባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ ከግዲያው ቀደም ባሉት ቀናትም እነዚሁ ፖሊሶች በሟች አቶ ብርሃኑና ሌሎች የመድረክ አባላት ላይ ግዲያ እንደሚፈጽሙና ከአከባቢው እንደሚያጠፉዋቸው ሲዝቱ መቆየታቸውም ታውቋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ረቦ የ40 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እንዳልተፈጸመም ለማወቅ ተችሎአል፡፡
በ2007 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉ የሚወራለት የኢህአዴግ ካድሬዎች በአሁኑ ወቅት በምርጫው ቅስቀሳ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ የመድረክ አባላትን በየአከባቢው የማዋከብ፣ የማሰር፣ በገንዘብ የመቅጣት፣ የመደብደብና የመግደል ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን ከምርጫው ዕለት ጀምሮ ከተገደሉት የመድረክ አባላት አቶ ብርሃኑ ረቦ 4ኛው ሟች ናቸው፡፡ ቀደም ስል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ አቶ ጊዲሳ ጨመዳ፣ በምዕራበ አርሲ ዞን ቆራ ወረዳ አቶ ገቢ ጥቤ እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ትግራ ዞን በማይካድራ ከተማ አቶ ታደሰ አብርሃ የሚባሉ የመድረክ አባላት ከምርጫው ዕለት ጀምሮ መገደላቸው ይታወሳል፡፡ በምርጫው ወቅት መድረክ ጠንካራ እንቅስቃሴ ባደረገባቸው በደቡብ ብ/ብ/ሕ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ከምርጫው ወዲህ ብቻ ቤታቸው የተቃጠለባቸው፣ የፈረሰባቸው፣ በጥይት የቆሰሉ፣ በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውና በእስር በመሰቃየት ላይ የሚገኙት የመድረክ አባላት ቁጥር በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ነው፡፡

Ingen kommentarer:

Legg inn en kommentar