ዶ/ር መረራ የ11 ወር፣ ዶ/ር ዳኛቸው የ8 ወር ደሞዝ አልተከፈለንም አሉ
አሁንም በዩኒቨርሲቲው እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሣይንስ መምህሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ በመኖሪያ ቤትና በደሞዝ ጉዳይ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር እየተወዛገቡ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና የ11 ወር ደሞዛቸውን ተከልክለው ለ12 አመት ከኖሩበት የዩኒቨርስቲው ንብረት የሆነ መኖሪያ ቤት በ15 ቀናት ውስጥ እንዲለቁ የታዘዙ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋም የ8 ወር ደሞዛቸው ሳይከፈላቸው፣ ለ 7 አመት ከኖሩበት ቤት እንዲለቁ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡ ለ28 አመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማራቸውን የሚገልፁት ዶ/ር መረራ፤ ከወራት በፊት የዩኒቨርሲቲው የበላይ አስተዳደር ከዩኒቨርስቲው ጋር ያላቸው ውል መቋረጡን ቢያሳውቃቸውም የፖለቲካ ሣይንስ የሚያስተምሩበት የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ውሉን እንዳላቋረጠና የ2 አመት ኮንትራት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር ግን የማስተማር ስራቸውን
እንዳቆሙ አድርጐ ለ12 አመት ከኖሩበት መኖሪያ ቤት በ15 ቀናት ውስጥ እንዲለቁ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለቤቱ አገልገሎት ያልከፈሉትን 2300 ብር እዳ እንዲከፍሉም በደብዳቤው አሳስቧል፡፡ “ቤቱን ለመልቀቅ ሌላ ቤት እያፈላለግሁ ነው” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ለ11 ወራት ያስተማርኩበትን ደሞዜን አልከፈለኝም ሲሉ ያማርራሉ፡፡ አሁንም እያስተማርኩ ነው ያሉት ምሁሩ፤ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ነው እንጂ የማስተምርበት ኮሌጅ የኮንትራት ውሌን አላቋረጠም፤ ከኮሌጁ ጋርም የ2 ዓመት የኮንትራት ውል አለኝ” ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የ11 ወራት ደሞዛቸውን እንዲከፍላቸው ለፍ/ቤት አቤት ለማለት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምህራንን የመቅጠርም ሆነ የማባረር ስልጣን የበላይ አመራሩ ሳይሆን የኮሌጁ ነው ያሉት ዶ/ር መረራ፤ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር ጣልቃ ገብቶ ነው ደሞዜ የታገደው ብለዋል፡፡ የበላይ አመራሩ ህጋዊ ተግባር እንዳልፈፀመ በፅሁፍ ለዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራሮች ማሳወቃቸውንም ዶ/ሩ ተናግረዋል፡፡ “ከባድ የማግለል ተግባር እየተፈፀመብኝ ነው” የሚሉት ምሁሩ፤ የፕሮፌሰርነት ማዕረጌንም አላግባብ ተከልክያለሁ፤ የሲቪል ሰርቪስ ፍ/ቤት ለሚባል አካልም ጉዳዩን አመልክቼ ምላሽ እየተጠባበቅሁ ነው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለ7 ዓመት በፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህርነት ያገለገሉት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋም የዩኒቨርሲቲው ንብረት ከሆነው መኖሪያ ቤት ያለባቸውን 3300 ብር እዳ ከፍለው፣ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲለቁ መታዘዛቸው የሚታወስ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው ለዩኒቨርሲቲው የመልስ ደብዳቤ ፅፈው ምላሹን እየተጠባበቁ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ቤቱን በተመለከተ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጣቸው ለቀጣይ ሦስት ወራት ቤቱን እንደማይለቁ ተናግረዋል፡፡
“አንድ ባለስልጣን በጡረታ ሲገለል ሙሉ ጥቅማ ጥቅሙ ተከብሮለት ቢሆንም አንድ ትውልድ የሚቀርፅ የዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁ በቀላጤ ከምትኖርበት ውጣ መባሉ ያሳዝናል” ብለዋል ምሁሩ፡፡
የ8 ወራት ደሞዛቸውም እንዳልተከፈላቸውና እስካሁንም ከዩኒቨርሲቲው ህጋዊ በሆነ ደብዳቤ የስራ ውላቸው ስለመቋረጡ የደረሳቸው መልእክት እንደሌለ የሚናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው፤ የማስተማር ስራቸውንም ሙሉ ለሙሉ እንዳላቆሙ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል “የዳኛቸው ሃሳቦች” በሚል ርዕስ በታተመው መፅሃፍ “ሃሳቤን ተዘርፌያለሁ” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ በመፅሃፉ አዘጋጅ መሃመድ ሃሰን እና በአከፋፋዩ አቶ አስራት አብርሃ ላይ በከፍተኛው ፍ/ቤት ትናንት ክስ መመስረታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የመፅሃፉ አዘጋጅ መሃመድ ሃሰን ይቅርታ መጠየቁን የጠቆሙት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ሁለቱንም ግለሰቦች በወንጀል መክሰስ ያስፈለገው ለሌላውም መማሪያ እንዲሆን ነው ብለዋል፡፡ በመፅሃፉ 95 በመቶ
የሚሆነው ሃሳብ በተለያዩ ጊዜያት የተናገሯቸው፣ ያስተማሯቸው፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ ገለፃ የሰጡባቸውና በሰነድና በተለያዩ ፅሁፎች የተቀመጡ መሆናቸውን ያብራሩት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ለክሱ ማስረጃነትም እነዚሁ ሰነዶች ተያይዘው መቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡
go to link http://addisadmassnews.com/index.php?
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar