በያህያ ጀማል | March 23, 2014
የነፍጠኛው ገዢ መደብ ርዝራዦች በተቻላቸው ኣቅም ሁሉ ኦሮሞና ኦሮሞነትን ለመፋለም ተሰማርተዋል። የመንግስትን ስልጣን ይዞና የነፍጠኛውን የበላይነት ተክቶ ኣገር እየመራ ያለው ወያኔ ኢህኣዴግ ቢሆንም የነርሱ ዋነኛ ጠላት ግን ዛሬም ስልጣን ኣልባው ኦሮሞ ሆኖ ቀጥሏል። የወያኔ ኢህኣዴግ መንግስት ኦሮሞን ጨምሮ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ኣምኖ መቀበሉና ይህንንም (በመጠኑም ቢሆን) የሚያረጋግጥ ፌዴራላዊ ስርኣት መዘርጋቱ ያበገናቸው የቀድሞው ኣሃዳዊ ስርኣት ናፋቂዎች ኣማራ ነን ብለው ኣፋቸውን ሞልተዋ እንደ ኣማራ ብሄር ቆመው ከመከራከር ይልቅ ዛሬም በ ‘ኢትዮጵያነት’ የማስመሰያ ካባ ነጻ ህዝቦችን መልሰው መዳፋቸው ስር ማስገባት ከማለም ኣልቦዘኑም። ዛሬም የኦሮሞው፣ የትግራዩ፣ የሲዳማው፣ የቤኒሻንጉሉ፣ የሃዲያው ወዘተ ማንነት በራሳቸው ማንነት ታፍኖ፣ ቁዋንቁዋቸው በኣማርኛ ተተክቶ ኣማራ ሆይ ማረን ብለው ኣጎንብሰው ኣንዲያመልኩኣቸው ከማለም ኣልተመለሱም።
እነዚህ የነፍጠኛው ገዢ መደብ ኣተላዎች በነርሱ እኩይ የስልጣን ጥማትና በሌሎች ላይ በሚያሳዩት ንቀት ሳቢያ ኣማራውን ሁሉ ኣንድ ላይ ደምረን እንድንጸየፍ ወይም እንድናወግዝ ይፈልጋሉ። በርግጥ የተከበረው የኣማራ ህዝብ እነዚህን ከኣብራኩ የወጡና ለሌሎች ሰላምና ነጻነት ጸር የሆኑትን ልጆቹን ገስፆ የማስታገስ ሃላፊነት የወደቀው ከማንም በላይ በገዛ ትከሻው ላይ መሆኑ ኣይካድም። ኣንዳንድ መረን የለቀቁ ተማርን ባይ የኣማራ ተወላጆች ጭራሽ በነርሱ ብሶ ‘ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ16ኛው ክፍለ ዘመን ነው’ እያሉ ኣደገኛ ድፍረት እያሳዩን ናቸው። የተከበረው የኣማራው ህዝብ እንዲህ ባለው ኣደገኛ ድፍረት ውስጥ እጁን ከማስገባት ኣንዲቆጠብና የህዝብ ለህዝብ ክብራችንን እንደጠበቅን እንድንዘልቅ እየተመኘን ከመዘዘኞቹ ባለጉዳዮች ጋር የታሪክና የፖለቲካ ሂሳባችንን ለማወራረድ እንገደዳለን።
የኣማራው ሊህቃን ስለ ምኒልክ ጭፍጨፋና ስለ ኢትዮጵያ ኢምፓየር ኣመሰራረት ኢ ፍትሃዊነት በተነሳ ቁጥር እሱን ትተው ዘለው ቂብ የሚሉት በ16ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ጉዳይ ላይ ነው። ለምኒልክ ጉዳይ ምኒልካዊ ምላሽ መስጠት ተስኖኣቸው ሃራምባና ቆቦ የሆነ ነገር መዘባረቁ ይቀናቸዋል። ምኒልክ የራሱን ኢምፓየር ለመመስረት ሲዘምት ኦሮሞውንና ሌላውን ብሄር ጨፍጭፏል ኣልጨፈጨፈም ነው ጥያቄው። ምላሹም ኣዎን ጨፍጭፎ ነበር ወይም የለም እልጨፈጨፈም ነው። ከሁለቱ መልሶች የተያዘውን ይዞ በጭብጥ መከራከር ያባት ሆኖ ሳለ ሮጠው 16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ጉብ ማለት ኣስቂኝ የፈሪዎች ባህሪይ ነው።
ትምህተኞቹ የነፍጠኛ ልጆች የምኒልክን ጭፍጨፋ በተመለከተ ‘ኣባቶቻችን ስህተት ፈጽመዋልና ያለፈውን ስህተታቸውን ለታሪክ ትተን በኣዲስ ወዳጅነት ለወደፊቱ የጋራ ህልውናችን እንትጋ’ የሚል በቅን የተሞላ ኣቁዋም ይይዙ ይሆናል ተብለው ሲጠበቁ ይባስ ብለው ‘ጭፍጨፋው ፍትሃዊ ነበር’ እያሉ ሽንጣቸውን ገትረው መከራከርን መርጠዋል። ይህ ኣጉል ድፍረታቸው ደግሞ የሚመነጨው ‘ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በሁዋላ ነውና እንዲህ ኣይነት ወቀሳ ሊያቀርብብን ሞራል የለውም’ ከሚል የድንቁርና እምነታቸው ነው። ኢትዮጵያን የያዛችሁት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በመሆኑ እኛ የጥንት ባለርስቶች ስንጨፈጭፋችሁ መጨፍጨፍ፣ ስንገዛችሁ መገዛት፣ ስናፍናችሁ መታፈን እንጂ ሌላ ኣማራጭ የላችሁም ሊሉን ይዳዳቸዋል። ከዚህም ኣልፎ ወራሪውን ምኒልክን ሲታገሉት የወደቁ የኦሮሞ ጀግኖችን ያላንዳች ሃፍረት ‘ከሃዲዎች’ ሲሏቸውም እየሰማን ነው። የምኒልክ ጦር ዘምቶ የያዘው መሬት ጥንታዊ መሬታችን እንጂ የኦሮሞ መሬት ኣልነበረምና በዚህ ጦርነት ላይ ኦሮሞውን ጡት መቁረጥና መስለብ ፍትሃዊና ቁዱስ እርምጃ ነው እያሉ ናቸው። ይህ ነው የመከራከሪያቸው ዋነኛው ጭብጥ።
ይህን ካልን ዘንዳ ወደ ዋናው ነጥብ እንግባ። ለመሆኑ ኦሮሞ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ኣገሩ ሌላ ነበር? ይህንን ኣስቂኝ ጥያቄ ለመመለስ ሲባል ወደ ጥንታዊ ታሪክ መግባት የግድ ሊሆንብን ነው። ጥንታዊው ታሪክ ስንል ቢያንስ ከኣንድ ሺህ ኣመት በፊት ስለነበረው ታሪክ ማለት ነው። ጥንታዊውን ታሪክ ስናስብ ዛሬ ኦሮሞ፣ ኣማራ፣ ወዘተ እየተባሉ በብሄር ስም ስለሚጠሩ ህዝቦች ሳይሆን የነዚህ ብሄሮች ኣባት ስለነበሩት ነገዶች ነው የምናነሳው። የቀጣናችን ጥንታዊ ታሪክ ስለ ብሄሮች ሳይሆን ስለነገዶች ነው የሚያወሳው። በነገድ ነገዳችን ስንደለደል ታዲያ ኦሮሞ ዋነኛው የኩሽ ነገድ ግንድ መሆኑን እናገኛለን። የኩሽ ነገድ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ (የዛሬዋን የምኒልክ ኢምፓየር ማለቴ ኣይደለም) የስልጣኔ ባለቤት ነው። የኩሽ ኢትዮጵያ ግሪኮቹ Aithiops ያሉዋት የጥቁር ህዝብ ምድር ነበረች። ይቺ የኩሽ ኢትዮጵያ ናት በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚኣብሄር ትዘረጋለች’ ተብላ የተጠቀሰችው። ይህ ደግሞ ከግብጽ ጀምሮ እስከ ኑቢያ ድረስ እንዲሁም በኣንዳንድ መልኩ ኣክሱምን የሚያጠቃልል የጥንት ስልጣኔ ኣሻራ ነው። በዚህ የስልጣኔ ዘመን ኣማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ… የሚባል የብሄር ኣደረጃጀት ላይ ኣልተደረሰም ነበር ብለናል። ስለሆነም ኩሾቹ ኣንደኩሽነታቸው፣ ሃበሾችም (ሁዋላ ላይ ከኩሽ ህዝብ ጋር የተዋሃዱ) እንደ ሃበሻነታቸው የራሳቸው የሆነ መለያ ታሪክ ነበራቸው። መካድ የማንችለው ትልቁ እውነታ ግን ግሪኮቹ ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ የሰጡት ምድር የኩሽ ምድር መሆኑና ኦሮሞ ደግሞ የኩሽ ነገድ ትልቁ ግንድ መሆኑን ነው። ይህ ሰፊ ምድር ደግሞ የዛሬዋን የምንሊክ ኢምፓየር ጨምሮ ኣብዛኛውን የምስራቅና ሰሜን ምስራቅ ኣፍሪቃን የሚያጠቃልል ነው።
ኦሮሞ የኩሽ ነገድ ዋነኛው ግንድ እንደመሆኑ መጠን ማናቸውም የኩሽ ስልጣኔ ኣሻራዎች የራሱ ናቸው። ኦሮሞ ኣሁን የምኒልክ ኢምፓየር ሆና ከተመሰረተችው ኢትዮጵያ ውስጥም ውጭም ሲኖር ነበረ። ሲሻው ሲወጣ ሲሻውም ሲገባ ነው የኖረው። ምክንያቱም መሬቱ ከጥንትም ጀምሮ የነገዱ የኩሽ መሬት ነውና በፈለገው ጊዜ ለመውጣትም ሆነ ለመግባት የማንም ፈቃድ የሚያሻው ኣልነበረምና። ይህ ደግሞ በማናቸውም የኣለም ህዝቦች ታሪክ ውስጥ የሚታወቅ ህዝባዊ ኣኗኗር ነው። ኣለማችን እንደዛሬው የፖለቲካ ድንበሮች ተበጅተው ኣንዱ ኣገር ከሌላው ተለይተው ሳይታወቁ በፊት ህዝቦች እንዳሻቸው ከስፍራ ስፍራ ሲንቀሳቀሱ ኖረዋል። በዚያ ላይ ኦሮሞ ጥንት ከብት ኣርቢ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ለከብቶቹ ግጦሽ ፍለጋ የኣየር ሁኔታው እንደቀናው በስፋት የመንቀሳቀስ ፍላጎት ነበረበት።
በነጻ ህዝቦች ንቀት የተጠናወቱት የነፍጠኛው ልህቃን ማወቅ ያለባቸው ሌላው ትልቁ ነገር እነርሱ የታሪክ ሃብታሞች ሆነው ኦሮሞው የታሪክ ድሃ ኣለመሆኑን ነው። እነርሱ የጥንት ስልጣኔ ባለቤቶች ሆነው ኦሮሞው ስልጣኔ ኣልባ ህዝብ ኣለመሆኑንም ጭምር ማስታወስ ኣለባቸው። የኦሮሞ ህዝብ ስልጣኔ በሁለት መልኩ ይገለጻል። ኣንደኛውና ኣንጋፋው በኩሽ ስልጣኔ ስም ኣለም የሚያውቀው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ስልጣኔ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከዚያ ጥንታዊ ዘመን በሁዋላ እንደ ብሄር ይዞት እስከ ዛሬ የዘለቀው ዴሞክራሲያዊው የገዳ ስርኣትና የስነ ከዋክብት ጥናት (Urjii Dhaha) ስልጣኔው ነው። ኦሮሞ በኩሽነቱ የነኑቢያና ኬሜት (ጥንታዊት ግብፅ) የግንባታና የስነፅሁፍ ስልጣኔዎች ባለቤት ነው። እንደ ሁዋለኛው ዘመን ኦሮሞነቱ ደግሞ ኣፍሪቃ ውስጥ በምሳሌነቱ የሚጠቀሰው የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መገለጫ የሆነው የገዳ ስርኣት ስልጣኔ ባለቤት ነው። ኦሮሞ በገዳ ስርኣቱ መሪውን (ኣባገዳውን) በሰላማዊ መንገድ ሲመርጥና ሲሸኝ፣ ከዚያም በታች ያሉትን ኣስተዳዳሪዎቹን ያላንዳች ደም ጠብታ ሲሾምና ሲሽር ኣለማችን ላይ ህዝቦች በስልጣን ጥም ደም ሲፋሰሱ ኖረዋል። ይህ እንደ ኦሮሞነታችን የምንኮራበት የስልጣኔያችን ዋልታ ሲሆን ለሌሎችም ጎሮቤቶቻችን በምሳሌነቱ የሚጠቀስና እንዲሁም እንደ ጉዲፈቻችን ሁሉ በተውሶ ስራ ላይ መዋል የነበረበት እንጂ በትምክህት መንቁዋሸሽ የሚገባው ባህል ኣይደለም።
ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ የዛሬዋ የምኒልክ ኢምፓየር ኢትዮጵያም የኦሮሞውና የሌላው ኩሽ ህዝብ ሁሉ መፍለቂያና መኖሪያ መሆኗን ልናሰምርበት እንሻለን። እኛ ትምክህተኞቹ የነፍጠኛ ልጆች የኣገሬውን ኣንጋፋ ህዝብ ኦሮሞውን ‘ኣገርህ እዚህ ኣይደለም’ ስላሉት ተረብሸንና ተርበትብተን ‘እናንተም ከደቡብ ኣረቢያ ቀይ ባህርን ኣቁዋርጣችሁ በመምጣት እዚህ የኛ ኩሽ ኣገር ላይ ሰፍራችሁኣልና ለቃችሁ ውጡልን’ እስከ ማለት ኣንሄድም። ትልቁ ጥያቄያችን የትላንትናው የታሪክ ጥያቄ ሳይሆን የዛሬው የፖለቲካ መብት ጥያቄ ነው። የዛሬው የፖለቲካ መብታችን በትላንትናው ታሪካችን ልክ እንዲሰፋልንም ኣንገደድም። ኣብዛኛው የኣለማችን ህዝብ በታሪክ ማንነቱ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ኣይደለም የፖለቲካ ኣስተዳደሩን ያዋቀረው።
ይህን ስንል የኣማራ ልህቃን በኣኩይነታቸው ገፍተው ኦሮሞ ኣገሩ እዚህ ኣይደለም የሚል የደንቆሮ ጨዋታ ከቀጠሉበት እኛም ምላሽ ይኖረናል። ኣማራው ማነው፣ ኣገሩስ የት ነው የሚለው ጥያቄ ሊከተል ይችላል። የዚህ ጥያቄ ምላሽ ደግሞ በእጅጉ መልሶ የሚጎዳው ኣሳ ጎርጉዋሪዎቹን የነፍጠኛ ልህቃንንና መከረኛውን የኣማራ ህዝብ ይሆናል። ስለሆነም ዶሮ ጭራ ጭራ… እንዲሉ የምኒልክ ልጆች በገዛ ሰውነታቸው ላይ እባብ ከመጠምጠም እንዲቆጠቡ ኣክመራለሁ።
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar