ሰዉዬዉ ቁጭ ብለው ሌሊት-ሌሊት ያሰባሰቧቸዉን የፈጣን ሎተሪ ቲኬታቸዉን እየቀያየሩ ሲፍቁ፣ ሲያስፍቁና ከሎተሪ መዉጫዉ ጋር ሲያመሳክሩ ያድሩ ነበር አሉ። እናማ አንደኛዉን ሲሞክሩት ውጤቱ ሌላ ነዉ። በሌላኛዉ ቢመኩም የባሰበት ሆነ! ሌላም ቢተካ ተስፋ ዬለውም። ላይተዉት ነገር የቤቱ ምሰሶና ማገሩ ‘በፈጣን ሎተሪዎቹ’ ተስፋ ላይ የተዋቀሩ ናቸዉ። አንዱ ሲጣል በሌላዉ ሲተካ ዉጤቱ እየራቀ ተስፈዉም እየመነመነ ቤቱ አልጸና ብሏቸዉ ላይ-ታቹን ሲኳትኑ በእልህ የመጨረሻ ዕድል ለመሞከር ባሕር ማዶ ድረስ ተሻግረዉ ታላቁን ‘ቶምቦላ’ በዉድ ዋጋ ይጋዛሉ። ዕድሉ ቀንቶኣቸው እነዚያን ‘ፈጣንና ፈጣጣ’ ሎተሪዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ አራግፈዉ ለመገላገል ተመኙ። ግን ክፉ ዕድል ሆኖ ብዙ የደከሙለትን ‘ቶምቦላ’ መጨረሻዉን ለማየት ሳይታደሉ የመሄጃ ጊዜያቸዉ ደረሰና የያዙትን ሁሉ ለዘመድ አዝማዶቻቸዉ በዉርስ ሰጥተዉ ይሰናበታሉ።
የሰዉዬዉ ወራሾችም የነገሩን አያያዝ አልቻሉበትምና አንዱን ሲይዙ ሌላዉ እየሸሸ ገና ከጅምሩ በሰዶ- ማሳደድ ጨዋታ ልባቸዉ ዉልቅ ይላል። “ልፋ ያለዉ በህልሙ ዳዉላ ይሸከማል” ይባል የል! ዉድ ዋጋ የተከፈለበትና እጅግ የተደከመበት ታላቁ ሎተሪም ገና ተፍቆ ሳይፈተሽ ዉጤቱ ከወዲሁ ባለማማሩ ከመጠቅለያዉ እንኳ በወጉ ሳይገለጥ እንደተሸፋፈነ ወደመጣበት መልሰዉታል። ፈጣኖቹም ቢሆኑ ኣንድ በኣንድ እየተመዘዙ ሲፋቁና ሲጣሉ የተቀሩት ደግሞ አንዳችም ተስፋ የሚጣልባቸዉ ባለመሆናቸው የሰዉዬዉ ቤት ግድግዳዉ ተንዶ ጣራዉ ሊፈራርስ የቀናት ዕድሜ ቀርተዉታል።
ጎበዝ! በዚህ ወቅት ብርቱ ጉዳዮች ኣሉብን። ለሕዝባቸዉ ነጻነትና ክብር የወደቁ ጀግኖቻችንን እናስባለን። የተያያዝነዉን ትግል ለማፋጠን ደግሞ ራሳችንን የበለጠ እናዘጋጃለን። ስለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ሲሰሙ የሚያምማቸዉን ደግሞ ጠንካራ ዉጋት እየለቀቅን የባሳ እናቃዣቸዋለን። ስለዚህም በፍጥነት ወደ ጉዳዬ ልዝለቅ!
አንድ ሕዝብ ነጻነት ከሌለዉ ህሊዉናዉ አደጋ ላይ ይወድቃል። ይህ መሰል ኣደጋ የተጋረጠበት ሕዝብ ራሱን ከመከላከል የቀደመ አሳሳቢ ጉዳይ አይኖረዉም። ለዚህም ነዉ የዚህ ዓይነቱን አደጋ መከላከል ዉዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር የሚሆነዉ። ለዚህ ዓይነቱ ግዴታ ሕዝቡ የጋራ ኃላፊነት ይኖረዋል። ይህን ሃላፊነት ለመወጣት መሪዎችንና አመራሮችን በየደራጃዉ ይሰይማል። የፖለቲካ ፕሮግራሞችን ይነድፋል። ኣዋጭ የሆኑ የትግል ስልቶችን ይቀይሳል። አሳታፊና ዉጤታማ የትግል መዋቅሮችን ይዘረጋል። ኃይሉንና ጉልበቱን ያቀናጃል። ነጻነት ያለመስዋዕትነት በነጻ ኣይገኝምና ትግሉ የሚጠይቀዉን መስዋዕት ሁሉ ያቀርባል። ይህ በሕዝቡ ፍላጎትና ዉሳኔ ብቻ የሚሆን እንጂ ከየትኛዉም ኃይል ፍላጎትና ተጽዕኖ አንጻር የሚመዘንና የሚመጠን አይደለም። እንደዚያ ሊሆንም አይችልም። ጂቱ ለሚ
Ingen kommentarer:
Legg inn en kommentar